ታህሳስ 13፣ 2022 የአጭር ጊዜ ስልጠና መርሃ ግብር የመጨረሻ ቀን በመሆኑ የስልጠና ተሳታፍ ቡድኑ እንደ መጀመሪያው ቀን በኪዮቶ ዩንቨርስቲ ሴሚናር ክፍል ውስጥ በመሰብሰብ የስልጠናውን ማጠቃለያ አውደ ጥናት አካሄዷል። በማጠቃለያ ውይይቱ ላይ ከሚያዛኪ ዩኒቨርሲቲ እና ከኪዮቶ ዩኒቨርሲቲ የMNGD ፕሮጀክት አባላትም በበየነ መረብ ተሳትፈዋል።
የማጠቃለያ አውደ ጥናት አቀራረቡ በአራት ቡድን የተከፈለ ሲሆን በመጀመሪያ ዶ/ር ፍፁም የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ/አ.አ.ሳ.ቴ.ዩ/ ፕሮፌሰሮችን በመወከል ገለጻ አቅርበዋል፡፡ በመቀጠልም አቶ ይታየው የ አ.አ.ሳ.ቴ.ዩ ወጣት ተመራማሪዎች ቡድንን በመወከል ገለፃ አድርገዋል። ከአቶ ይታየው ቀጥለው ገለጻ ያቀረቡት የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኩሴ እና ከኢትዮጲያ መንገዶች ባለስልጣን የመጡት ወ/ሮ እህተ ነበሩ፡፡ ከገለፃው በኃለ በስልጠናው ያገኙትን እውቀት በቀጣይ በኢትዮጵያ በሚያደርጉት ስራ እና በMNGD የፕሮጀክት ላይ እንዴት ተግባራዊ እንደሚያደርጉ ተወያይተዋል። ምንም እንኳን የሁለት ሳምንቱ የስልጠናው መርሃ ግብሩ በተጣበበ የጊዜ ሰሌዳ የተካሄደ ቢሆንም፣ ተሳታፊዎች በተቻለ መጠን ከእያንዳንዱ አጋጣም ለመማርና ልምድ ለመቅሰም ሲያደርጉ የነበረው ጥረት በጣም አስደናቂ ነበር።
በመጨረሻም የኪዮቶ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ፕ/ር የሺጌታ የፕሮጀክታችን ትኩረት በመሆኑ በቀጣይ በግንኙነት /“networking” / ላይ የበለጠ ትኩረት በማድረግ ተግባራቸው እንዲያከናውኑ የስልጠናውን ተሳታፊዎች በማበረታታት ለ14 ቀናት የቆየው የአጭር ጊዜ የስልጠና መርሃ ግብር በተሳካ ሁኔታ ተጠናቋል።